ትራምፕ፣ መስክ እና ቢል ጌትስ፡ አዲስ የተለቀቀው የኤፕስቲን ፋይል ምን ይዟል?

ኢላን መስክ፣ የእንግሊዙ ፖለቲከኛ ማዲልሰን እና ኤፕስቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters/BBC/Getty

የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ከሟቹ የወሲብ ጥቃት ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፋይሎችን ይፋ አድርጓል።

ፋይሎቹ 3 ሚሊዮን ገፆች ያሉት ሲሆን 180 ሺህ ፎቶዎች እና 2 ሺህ ቪዲዮዎች አርብ ዕለት ተለቀዋል።

መዛግብቱ ጄፍሪ ኤፕስቲን እስር ቤት ሳለ የነበረበትን ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታ እና ከኤፕስቲን ጋር በመተባበር ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴቶችን ታጓጉዝ የነበረችው ጊሌይን ማክስዌልን የምርመራ ውጤት የያዙ ናቸው።

ኤፕስቲን ስማቸው ከገዘፈ ሰዎች ጋር ያደረጋቸው የኢሜይል ልውውጦችም ይፋ ተደርገዋል።አብዛኛዎቹ ኢሜይሎች ከ10 ዓመት በፊት የተፃፉ ሲሆኑ ክስ ቀርቦበት ሳለ የተለዋወጣቸው ናቸው።

ኤፕስቲን በአውሮፓውያኑ 2008 ፍሎሪዳ ውስጥ ተፈርዶበት እስር ቤት ውስጥ ሳለ ነሐሴ 2019 መሞቱ ይታወሳል።

ኤፕስቲን ከእንግሊዙ ልዑል ጋር ያደረገው ልውውጥ

ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" ከተባለ ግለሰብ ጋር ያደረገው የኢሜይል ልውውጥ ይፋ የተደረገ ሲሆን ግለሰቡ የቀድሞው የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው እንደሆነ ይታመናል። ሁለቱ ግለሰቦች በባኪንግሀም ቤተ-መንግሥት "ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ" እራት እንደበሉ የኢሜይል ልውውጣቸው ያሳያል።

በሌላ መልዕክት ኤፕስቲን "ዘ ዱክ" የተባለውን ግለሰብ ከ26 ዓመት ሩሲያዊት ጋር ለማስተዋወቅ ሲሞክር ያሳያል።

ግለሰቦቹ መልዕክት የተላላኩት በአውሮፓውያኑ 2010 ሲሆን ይህም ኤፕስቲን 18 ዓመት ያልሞላትን ታዳጊ ለወሲብ ማታለሉን ካመነ ከ2 ዓመት በኋላ ማለት ነው። ኤፕስቲን በወቅቱ በቁም እስር ላይ ነበር።

ከኤፕስቲን ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያት የልዑልነት ማዕረጉን የተነጠቀው አንድሪው አንዲት ሴት መሬት ላይ ተኝታ እሱ ተንበርክኮ ሲመለከታት የሚያሳይ ፎቶም ተለቋል።

የኢሜይል ልውውጦቹ በወንጀል ሊያስከስሱ የሚችሉ አይደሉም።

አንድሪው ከአንዲት ሴት ጋር የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice

በርካታ ጊዜ ስማቸው የተነሳው ትራምፕ

አዲስ በተለቀቁት ፋይሎች ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስም በርካታ ጊዜ ይነሳል።

ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም ፕሬዝደንቱ ግን ጓደኝነታቸው ከበርካታ ዓመታት በፊት እንደተቋረጠ እና ስለኤፕስቲን የወሲብ ወንጀል የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።

መዛግብቱ ግን ፕሬዝደንት ትራምፕ እና ኤፕስቲን እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ላይ የቀረቡ የወሲብ ውንጀላዎችን ይዘዋል።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ጥፋት እንደሌለባቸው የሚናገሩ ሲሆን ከግለሰቡ ሰለባዎች ጋር በተያያዘ እስካሁን ክስ አልቀረበባቸውም።

በቅርቡ የተለቀቁትን ፋይሎች በተለመከተም ዋይት ሐውስ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

"አንዳንዶቹ ሰነዶች ፕሬዝደንት ትራምፕ ላይ እውነተኛ ያልሆኑ ወቀሳዎችን የያዙ ናቸው። እነዚህ ወቀሳዎች ከ2020 ምርጫ በፊት ለኤፍቢአይ ምርመራ ቀርበዋል" ሲል የፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል።

"ግልፅ ለመሆን እነዚህ ወቀሳዎች መሠረት የሌላቸው እና ሐሰተኛ ናቸው። ቅንጣት ያክል ተዓማኒነት ቢኖሯቸው ኖሮ ትራምፕ ላይ ይነጣጠሩ ነበር" ሲል መግለጫው አክሏል።

ኢላን መስክ እና ኤፕስቲን

አርብ የተለቀቁት ሰነዶች ኤፕስቲን እና የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃሩ ኢላን መስክ ያደረጓቸውን የኢሜይል ልውውጦችም ይዘዋል።

ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ክስ ያልቀረበበት መስክ ከዚህ ቀደም ኤፕስቲን ወደ ደሴቱ መጥቶ እንዲጎበኘው ቢጠይቀውም ይህን እንዳልተቀበለ ይናገራል።

አሁን የተለቀቁት ኢሜይሎች እንደሚያሳዩት መስክ ከአንድ ጊዜ በላይ የኤፕስቲን ደሴትን ለመጎብኘት ጥያቄ አቅርቧል።

በአውሮፓውያኑ 2012 ኢላን መስክ ለኤፕስቲን በላከው መልዕክት "የትኛው ቀን/ምሽት ነው የቀለጠው ፓርቲ የሚካሄደው?" ሲል ይጠይቃል።

በሌላ 2012 በተላከ መልዕክት ደግሞ ኤፕስቲን በሄሊኮፕተር ምን ያህል ሰዎች ወደ ደሴቱ እንደሚመጡ ሲጠይቅ መስክ እሱ እና በወቅቱ ሚስቱ የነበረችው ታሉላህ ራይሊ ብቻ እንደሚመጡ ይመልሳል።

በ2012 በገና በዓል ቀን የተላከ መልዕክት መስክ "ፈታ ማለት እፈልጋለሁ" በማለት ኤፕስቲን ፓርቲ አዘጋጅቶ እንደሆነ ይጠይቀዋል።

በ2013 የተላኩ ሌሎች ኢሜይሎች ላይም መስክ እና ኤፕስቲን ወደ ደሴቱ ስለሚደረጉ ጉዞዎች ያወራሉ።

ኢላን መስክ ወደ ኤፕስቲን ደሴት ተጉዞ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ግን የሉም።

መስክ ቅዳሜ በኤክስ ገፁ "[ከኤፕስቲን] ጋር የተደረጉ የኢሜይል ልውውጦች እንደወጡ አውቃለሁ፤ በክፉ ተተርጉመው ስሜን ለማጥፋት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ" ሲል ጽፏል።

"እኔ እሱ አያሳስበኝም። የሚያሳስበኝ ከኤፕስቲን ጋር በመሆን ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ለፍርድ አለመቅረባቸው ነው። በተለይ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴቶችን የበዘበዙ ሰዎች" ሲል አክሏል።

ጄፍሪ ኤፕስቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢል ጌትስ ላይ የቀረበው ወቀሳ

የቢል ጌትስ ቃል አቀባይ በቅርቡ የተለቀቁት የኤፕስቲን ፋይሎች ያወጡትን ወቀሳዎች አጣጥለዋል።

ቃል አቀባዩ ጌትስ በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ይዞታል የሚሉ እና ሌሎች ወቀሳዎችን "ፍፁም ውሀ የማያነሱ እና ሐሰተኛ" ናቸው ብለዋል።

ሁለት በ2013 በኤፕስቲን የረቀቁ ኢሜይሎች ከራሱ ወደ ራሱ የተላኩ ሲሆኑ ከጌትስ ጋር የተያያዘ የኢሜይል አድራሻ አይታይባቸውም።

አንደኛው ኢሜይል ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የመልቀቂያ ደብዳቤ ሲሆን ለጌትስ "ከሩሲያዊያን ሴቶች ጋር በተደረገ ወሲብ ምክንያት" ለመጣ በሽታ መድኃኒትን የተመለከተ አንቀፅ ይዟል።

ሌላኛው ኢሜይል ደግሞ "ውድ ቢል" ብሎ ጀምሮ ከጌትስ ጋር የነበረው ጓደኝነት ስለመቋጨቱ እና ጌትስ በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ከቀድሞው ሚስቱ ሜላንዳ ጭምር ለመደበቅ መሞከሩን ይናገራል።

የጌትስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ "እነዚህ ወቀሳዎች ሐሰተኝነቱ ከተመሰከረለት ግለሰብ የመጡ ውሀ የማያነሱ እና ፍፁም ሐሰተኛ የሆኑ ናቸው" ብለዋል።

ኤፕስቲን ከሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ያደረጋቸው የኢሜይል ልውውጦች ይፋ የተደረጉ ሲሆን ተጨማሪ ፋይሎች ስለመኖራቸው ግልፅ አይደለም።

ዲሞክራቶች የፍትሕ ሚኒስቴር ሌሎች 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ፋይሎችን ያለ ምንም ማብራሪያ አሁንም አልለቀቀም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ብዙዎች የፍትሕ ሚኒስቴር ሀብታም እና እጃቸው ረጅም የሆኑ ሰዎችን ስም ለመጠበቅ ሲባል አሁንም ያልተለቀቁ ሰነዶች አሉ ሲሉ ይከራከራሉ።